loading
በሩዋንዳ በአኖካ ዞን 5 የአትሌቲክስ ውድድር በድል የተመለሰው ልዑክ አቀባበል ተደረገለት

ለመጀመሪያ ጊዜ በአኖካ ዞን 5 እና በሩዋንዳ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስተናጋጅነት በ5 ስፖርት ሩዋንዳ ላይ በተካሄደውና በአትሌቲክስ ስፖርት በሰባት አትሌቶች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑክ ቡድን ዛሬ ማለዳ 12፡00 ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

ቡድኑ በ4 ወርቅ፣ 2 ብር እና 1 የነሀስ ሜዳሊያ በድምሩ 7 ሜዳሊያዎች በማግኘት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ፤ የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ያደረገውና በድል ለተመለሰው የኦሊምፒክ ልዑክ ቡድን ሀገሩ ሲገባ፤ በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣ የኮሚቴው ዋና ጸሀፊ አቶ ታምራት በቀለ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ እና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ ዶ/ር አሸብር ደስታቸውን በመግለፅ፤ ‹‹ ዞን 5 የምስራቅ አፍሪካ ውድድር እንደመሆኑ መጠን፤ በአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር ከፍተኛ ፍክክር ያለበት ነው፤ ሰባት ሆናችሁ ሰባት ሜዳሊያ በማምጣት የኢትዮጵያን ህዝብ አኩርታችኋል፤ እኛም ኮርተንባችኋል›› ብለዋል፡፡

በቀጣይም ሀገራችን ለሚኖራት አህጉር አቀፍ መላ አፍሪካ ጨዋታና ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ብርትታችሁ ስሩ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም አቅም በፈቀደ አግባብ እስከመጨረሻው ከጎናችሁ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ‹‹ጓደኞቻችሁ ዴንማርክ ላይ ባስመዘገቡት ድል ማግስት ይህንን ውጤት በማስመዝገባችሁ ኩርተናል በቀጣይም ለአህጉር አቀፍና አለም አቀፍ ዉድድሮች በርትታችሁ ስሩ ›› በማለት ገልፀዋል፡፡

ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር እና በሩዋንዳ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስተናጋጅነት ሲካሄድ በ5 የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ቴኳንዶ፣ የዉሃ ዳር መረብ ኳስ እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች እ.ኤ.አ ከሚያዚያ 2 – 6 በሩዋንዳ ኪጋሊ ተከናውኗል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በከፍተኛ ውጤት ለተመለሰው የኦሊምፒክ ልዑክ ዛሬ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት በኢትዮጵያ ሆቴል ይሰጣል ሲል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *