loading
በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ማንችስተር ዩናይትድ እና ዩቬንቱስ ተሰናብተዋል፡፡

የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ሁለት የመልስ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ተከናውነዋል፡፡

ወደ ስፔን ካታላን የተጓዘው ማንችስተር ዩናይትድ ካምፕ ኑ ላይ ባርሴሎናን ገጥሞ የ3 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዶ በአጠቃላይ ውጤት ከውድድሩ በ4 ለ 0 ውጤት ተሰናብቷል፡፡

ልማደኛው ሊዮኔል ሜሲ ለቡድኑ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር፤ ፊሊፕ ኮቲንሆ ቀሪዋን የባርሴሎና ግብ ከመረብ አገናኝቷል፡፡

በዚህም ባርሴሎና ከ2014-15 የቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በኋላ ለመጀመሪያ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ዙር ተቀላቅሏ፡፡

ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ በሁሉም ውድድሮች በ42 ጨዋታዎች 45ኛ ጎሉን ሲያስቆጥር በዚህ ዓመት 10ኛ የቻማፒዮንስ ሊግ ጎሉን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ነው፡፡

ማንችስተር ዩናይትድ በቀጣይ ዓመት የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ለማግኘት በሊጉ ቀሪ ጨዋታዎች በመጨረሻ አቅሙ መፎካከር ይኖርበታል፡፡

ባርሴሎና በቀጣዩ ዙር ከሊቨርፑል እና ፖርቱ አጠቃላይ አሸናፊ ጋር ይጫወታል፡፡

ጣሊያን ላይ ዩቬንቱስ በአሊያንዝ ስታዲየም የኔዘርላንዱን አያክስ አስተናግዶ ጨዋታው በእንግዳው ቡድን 2 ለ 1 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ በዚህም የውድድሩን ዋንጫ አብዝታ የምትሻው አሮጊቷ አሁንም ያደረገችው ሙከራ ከሽፎባታል፡፡

በክሪስቲያኖ ሮናልዶ አማካኝነት ዩቬ ቀዳሚ መሆን ቢችልም፤ ዶኒ ቫን ዴ ቤክ እና ወጣቱ አምበል ማቲያስ ዲ ላይት አያክሶችን ወደ ግማሽ ፍፃሜው ያበቁ ጎሎች ለቡድናቸው አበርክተዋል፡፡ አያክስ ከ1997 በኋላ ወደ ግማሽ ፍፃሚው ዙር ሲበቃ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ዛሬ የሚጫወቱት የማንችስተር ሲቲ እና ቶተንሃም አሸናፊ በግማሽ ፍፃሜው ከአያክስ ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *