loading
ደደቢት እግር ኳስ ክለብ ሌላ ቅጣት አስተናገደ

የደደቢት ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ጉዞ አሁንም ቀጥሏል፡፡

በ24ኛ ሳምንት የደደቢት እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ቅጣት አስተላልፏል፡፡

ግንቦት 03/2011 ዓ.ም በወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ እና በደደቢት እግር ኳስ ክለብ መካከል ሊደረግ የነበረው የ24ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ ላይ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በጨዋታው ቅድመ ስብሰባ እና በጨዋታው ሰዓት ባለመገኘቱ የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ ምዕራፍ ሶስት አንቀጽ 69 “ሀ” እና “ለ” በተደነገገው መሰረት፤ ለወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ሶስት ነጥብ እና ሶስት ግብ እንዲመዘገብለት ሆኖ ለደደቢት እግር ኳስ ቡድን ዜሮ ነጥብ እና ሶስት ግብ እዳ እንዲመዘገብበት፡፡

በተጨማሪ የደደቢት እግር ኳስ ቡድን ብር ስልሳ ሺህ (60,000.00) የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል፤ በአንቀጽ 69 ፊደል “ሐ” በተገለጸው መሰረት ለውድድር የቀረበውን ክለብ ወይም ልዩ ልዩ ወጪዎች በሚቀርበው ማስረጃ መሰረት የሚከፍል መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በዕለቱ ጨዋታ የሜዳ ገቢን በተመለከተ ደግሞ አወዳዳሪው አካል በጽሁፍ መጠኑን ገልጾ በሚልከው መሰረት እንዲከፍል እንዲደረግ፤ በአንቀጽ 69 በፊደል “መ” መሰረት የደደቢት እግር ኳስ ክለብ የቡድን መሪ ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ለስድት ወር እንዲታገዱ ተወስኗል ሲል ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ከቀናት በፊት ክለቡ ሜዳው ላይ ከፋሲል ከነማ ጋር ሲጫወት፤ ባጋጠመ የደጋፊ ረብሻ ምክንያት 150 ሺ ብር እና ሁለት የሜዳው ጨዋታዎቹን በዝግ እንዲያደርግ መቀጣቱ ይታወሳል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *