ኬንያዊያን ፖሊስ በንፁሀን ዜጎች ላይ የሚፈፅመውን ግድያ ያቁም የሚል ተቃውሞ እያሰሙ ነው::
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2 ፣ 2012 ኬንያዊያን ፖሊስ በንፁሀን ዜጎች ላይ የሚፈፅመውን ግድያ ያቁም የሚል ተቃውሞ እያሰሙ ነው:: በኬንያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተጣለውን የእንቅስቃሴ እገዳ ተከትሎ ፖሊስ ህግ በማስከበር ሰበብ በርካታ የሰብዓዊ መብቶችን እየጣሰ እንደሆነ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች ተናግረዋል፡፡ አልጀዚራ እንደዘገበው መንግስት እገዳውን ከጣለ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በፖሊስና በነዋሪዎች መካከል በተከሰቱ ግጭቶች ከ15 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡ በናይሮቢ ማታሬ በሚባለው የከተማዋ ክፍል ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰልፈኞቹ የኛ ህይዎት በዋጋ አይተመንምና ፈፅሞ እንዳይደገም የሚሉ መፈክሮችን ከፍ አድርገው ይዘው ተቃውሟቸውን ሲገልፁ ታይተዋል፡፡ የኬንያ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ፍሬድ ማቲያንጊ ያልተመጣጠነ ሀይል ተጠቅመው ያልተገባ ድርጊት የፈፀሙ ፖሊሶች መኖራቸውን አምነው ሁሉንም የፖሊስ አገልግሎት በጥቅሉ ጥላሸት መቀባት ግን ልክ አይደለም ብለዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ምንም እንኳ በአንዲት ጎስቋላ መንደር ውስጥ የምንኖር ብንሆንም ዓለም ድምፀችንን
እንደሚሰማው አንጠራጠርም ብለዋል፡፡