የኒጄሩ ፕሬዚዳንት ማማዱ ኢሱፎ የ2020 የሞ ኢባራሂም ሽልማት አሸነፉ::
አዲስ አበባ፣የካቲት 30፣ 2013 የኒጄሩ ፕሬዚዳንት ማማዱ ኢሱፎ የ2020 የሞ ኢባራሂም ሽልማት አሸነፉ:: ኢሱፉ ሽልማቱን ያገኙት በሀገራቸው የተከሰቱ በርካታ ችግሮች በቁርጠኝነት በመጋፈጥ ለህዝባቸው ጠቃሚ ስራ ሰርተዋል በሚል ነው፡፡ በተለይ በኒጄር ነፍጥ አንግበው ሽብር የሚፈጥሩ ሀይሎችን በመዋጋት፣ በርሃማነትን በመከላከል የልማት ስራዎችን በመስራት ረገድ አመርቂ ውጤት አስገኝተዋል ነው የተባለው፡፡
ፕሬዚዳንት ኢሱፉ ሀገራቸውን ለ10 ዓመት ካገለገሉ በኋላ ስልጣናቸውን እንደሚለቁና በምርጫ ያሸነፈ ሀገሪቱን እንዲመራ መወሰናቸውን ቀደም ሲል አሳውቀዋል፡፡ ኢሱፎ ቃላቸውን አክብረው በተቀመጣላቸው ጊዜ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸው ሀገሪቱ የመጀመሪያውን ዲሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር አድንድታደርግ አስችሏታል ተብሏል፡፡
በአፍሪካ ለህዝባቸው መልካም ስራ ለሰሩ መሪዎች በየአመቱ ሽልማት የሚያዘጋጀው ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ካሉት መስፈርቶች መካከል መልካም አስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜን አክብሮ ስልጣን ማስረከብ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የፋውንዴሽኑ የሽልማት ኮሚቴ ሊቀመንበር ፌስተስ ሞጌ በስነስርዓቱ ባደረጉት ንግግር ፕሬዚዳንት ኢሱፎ በሀገራቸው የነበረው የድህነት መጠን በሚታይ መልኩ መቀነሳቸውን መስክረውላቸዋል፡፡