ሃላፊዎች ሆይ ከታዩት ይልቅ ወዳልታዩት አተኩሩ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 02፣ 2014 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ኢትዮጵያንና ህዝቧን በሃቅ ማገልገልና ከልመና የማላቀቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው አሳሰቡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት "አዲስ ምዕራፍ በአገልጋይ መሪነት" በሚል መሪ ሃሳብ አዲስ ለተሾሙ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ስልጠና መስጠት በጀመሩበተ ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅትም ቀጣይነት ያለው የስራ ልምምድ ካዳበርን ኢትዮጵያን ተረጂ ሳይሆን የምትረዳ አገር ማድረግ እንችላለን ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያ ህዝብ እና ታላቋን ኢትዮጵያ ለማገልገል እድል የተሰጣችሁ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ልትደሰቱ ይገባል ብለዋል፡፡ አመራሮች ህዝብን ለማገልግል ባገኙት ታላቅ ዕድል ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለማሻገር እና በተግባር የተደገፈ ታሪክ ለመጻፍ መነሳሳት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ በሚያገለግሉበት ወቅት ከሌብነት ፍፁም ነፃ በመሆን ኢትዮጵያንና ህዝቧን በሃቅ፣ በቅንነት እና በታማኝነት በማገልገል ከልመና ለማላቀቅ አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ መስራት አለባችሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ትኩረት ያልተሰጣቸው ጉዳዮች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃላፊዎች ከታዩት ይልቅ ወዳልታዩት አተኩሩ ብለዋቸዋል። ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች ተገኝተዋል። ለከፍተኛ አመራሩ በመሰጠት ላይ የሚገኘው ስልጠና ማሳወቅን፣ ማነሣሣትን እና ለቡድን ስራ መዘጋጀትን ዓለማ አድረጎ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው ከሰልጠናው መጠናቀቅ በኋላም ከአመራሩ የማድረግ ጉጉት፣ ያወቀውን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆን እና የዓላማ ጽናት ይጠበቃል ብለዋል።