loading
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ለመገናኘት መጠየቃቸው ተነገረ::

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 25፣2014 ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ለመገናኘት መጠየቃቸው ተነገረ:: የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር በሞስኮ
ለመገኘት ቢጠይቁም እስካሁን ምላሽ አላገኙም ተብሏል።


ፖፕ ፍራንሲስ ለጣሊያኑ ኮሪየር ዴላ ሴራ ጋዜጣ እንደተናገሩት የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኪሪል ጦርነቱ ከሚያደርሰው አስከፊ ጉዳት እንዲገታ ሚናቸውን እንዲወጡ እንዲሁ ጥሪ አቅርበዋል። ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት በሩሲያ ኤምባሲ ጉብኝት ያደረጉት አቡነ ፍራንሲስ ለጋዜጣው እንደተናገሩት
ግጭቱ ከገባ ሦስት ሳምንታት በኋላ የቫቲካን ከፍተኛ ዲፕሎማት ለፑቲን መልእክት እንዲልኩላቸው መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።


በመልእክታቸውም ወደ ሞስኮ ለመሄድ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን ከክሬምሊን እስካሁን ምንም ምላሽ ባይሰጣቸውም አሁንም ጥያቄያቸውን ከማቅረብ ወደኋላ እንደማይሉ ጠቁመዋል፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ አክለውም ፑቲን በዚህ ጊዜ ይሄንን ስብሰባ ላይፈልጉት ይችሉ ይሆናል በማለት ስጋታቸውን የገለፁ ሲሆን ፤በጦርነቱ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ የጉዳት መጠን ሊገታ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ጦርነቱ ሀገራቱን አሁንም የህይወት እና ንብረት ዋጋ እያስከፈለ ሲሆን ሰላማዊ ሰዎችን ከግጭት አካባቢዎች ለማስወጣት የሚደረገው ጥረትም እምብዛም ውጤት እያስገኘ እንዳልሆነ ተነግሯል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *