loading
ቻይና የታይዋን የአየር መከላከያ ክልል ጥሳ በመግባት የጠብ አጫሪነት ተግባር እየፈጸመች ነው ስትል አሜሪካ ወቀሰች፡፡

አዲስ አበባ፣ግንቦት 23፣2014 ቻይና የታይዋን የአየር መከላከያ ክልል ጥሳ በመግባት የጠብ አጫሪነት ተግባር እየፈጸመች ነው ስትል አሜሪካ ወቀሰች፡፡ የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ 30 የቤጂንግ የውጊያ አውሮፕላኖች ወደ አየር ክልላችን ዘልቀው ገብተዋል፤ ከነዚህ መካከል ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ተዋጊ ጄቶች ናቸው ብሏል፡፡


ቻይና በታይዋን ሁለተኛውን ግዙፍ ወታደራዊ ቅኝት ያደረገችው ትንሿ ደሴት ከአሜሪካ ጋር በደህንነትና በፀጥታ ዙሪያ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ማሰቧ መሰማቱን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡ የቻይና እቅስቃሴ ዋሽንግተንን ያስቆጣ ሲሆን ከአሁን ቀደምም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ቻይና በታይዋን የባህር ወሽመጥ የምታደርገው ትንኮሳ የለየለት ፀብ ቀስቃሽ መሆኑን ደጋግመው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡


የታይዋኗ ፕሬዚዳንት ታይ ኢንግ ዌን በበኩላቸው የመከላከያ ኃይላቸው ከአሜሪካ ብሔራዊ ጥበቃ አባላት ጋር በትብብር የመስራት እቅዶች አለን ብለዋል፡፡ ይህ ትብብርም ለቀጠናው ሰላም ትልቅ ፋይዳ አለው ሲሉ ፕሬዚዳንቷ ቻይናን የሚያበሳጭ ንግግር ማድረጋቸውን አልጀዚራ በዘገባው አስነብቧል፡፡ ባለፈው ዓመት የቻይና አየር ኃይል ክልሏን በመጣስ ከ900 በላይ ወታደራዊ ቅኝት ማድረጉን የገለጸችው ታይዋን ይህን ስጋት ለመቀነስ አሁን ላይ ከዋሽንግተን ሰፊ ድጋፍ እንደምትፈልግ እየተነገረ ነው፡፡ ቤጂንግ በበኩሏ በአንድ ቻይና ፖሊሲ መሰረት ታይዋን የግዛቴ አንዷ አካል በመሆኗ አሜሪካን ጨምሮ ጣልቃ ለመግባት የሚፈልጉ ሀገራት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ደጋግማ ከማስጠንቀቅ ቦዝና አታውቅም፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *