ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 27፣ 2012 ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።ዩኒቨርስቲዉ ለአርትስ በላከዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ ከ5 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በሻምቡ ካምፓስ እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ ፕሮጄክቶች ያሉበት ደረጃ ተጎብኝተዋል።
የጉብኝቱ ዋና አላማም በመገንባት ላይ ያሉ እና ተገንብተው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ያሉበት ደረጃ በመገምገም የወደፊት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታቅዶ የተካሄደ መሆኑን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ ተናግረዋል።በጉብኝቱ የመምህራን መኖሪያ፤ የተማሪዎች ክሊኒክ፣ የኮምፒውተር ማዕከል፣ የተማሪዎች የመማሪያ፤ የመመገቢያና የመኝታ ህንጻዎች እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች የተጎበኙ ሲሆን የስራ ሂደታቸው እና ያሉበት ደረጃ አበረታች በመሆኑ አብዛኛው ፕሮጀክቶች ስራቸው ተጠናቆ ለ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተነግሯል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑንም ተጠቅሷል።ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ተብለው ከሚጠሩ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ሲሆን 38 ሺህ ተማሪዎችን በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ተቀብሎ በተለያየ የትምህርት ዘርፍ እያስተማረ እንደሚገኝ ዩኒቨርስቲዉ በላከዉ መግለጫ አስታዉቋል