የላልይበላ ከተማ አስተዳደር የገና በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጌያለሁ አለ::
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 28፣ 2013 የላልይበላ ከተማ አስተዳደር የገና በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጌያለሁ አለ:: የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላልይበላ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ነው የከተማ አስተዳደሩ የገለፀው፡፡ የቅዱስ ላልይበላን ዓመታዊ ክብረ በዓል ምዕምናንና ጎብኚዎች ወደ ሥፍራው መግባት ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል። ቅድስቲቷ ምድርም በምዕመናንና በጎብኝዎች ተውባለች።
የበዓሉን ዝግጅት አስመልክቶ ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የላልይበላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ይልማ መርቅ በዓሉን በስኬት ለማጠናቀቅ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የፀጥታና የመስተንግዶ ኮሚቴዎችን ጨምሮ ሰባት ኮሚቴዎች መኖራቸውን የተናገሩት ከንቲባው፤ የፀጥታው ጉዳይ አስተማማኝ እንዲሆን እንደተሠራና በዓሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ሃይሉ አስቀድሞ በመምከርና የአሠራር አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል። የፀጥታው ሁኔታ በየቀኑ እየተገመገመ ነው ያሉት ከንቲባው በስርቆት ተሰማርተው የተገኙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ መስተንግዶውም ከመቀበል ጀምሮ እስከ መሸኜት ድረስ የሚቀጥል ሲሆን የበዓሉ ታዳሚዎች
በቆይታቸው ወቅት ደስተኛ እንዲሆኑ ጥረረት ተደርጓል ነው የተባለው፡፡