loading
የሶማሊያው አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን በይፋ ተረክበው ስራ ጀመሩ፡፡

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 የሶማሊያው አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን በይፋ ተረክበው ስራ ጀመሩ፡፡ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ በስልጣን ርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግር አዲሱ መሪ ወደ ስልጣን የመጡበት ወቅት ፈታኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዓመታት በአልቃኢዳ መራሹ አልሸባብ የምትታመሰው ሶማሊያ በቅርቡ ያጋጠማት የድርቅ አደጋ ሌላው ራስ ምታት ነው ብለዋል ፋርማጆ፡፡


እናም ይህን ሁኔታ ለማስተካከል ፕሬዚዳንት ሀሰን ሸይክ ሞሐመድ ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው ስራቸውን እዲጀምሩም አሳስበዋል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው የተካሄደውን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ታሪካዊ በማለት የገለጹት ሲሆን ሁሉም ዜጋ ሀገሩን ዳግም ለመገንባት ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሸይክ ሞሐመድ አክለውም በእኔ ላይ እምነት ከጣላችሁና ስራዬ የተቃና እንዲሆን ካገዛችሁኝ የማንፈታው ችግር የለም ማለታቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሶማሊያ ልኡክ ጀምስ ስዋን ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ በሀገሪቱ የተካሄደውን ምርጫ አድንቀው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ስራዎች በመለየት በፍጥነት ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለሶማሊያ አዲስ የዴሞክራሲ ባህል በር ከፋች ነው ያሉት ልኡኩ በሀገሪቱ
ያሉትን ተደራራቢ ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የመንግስታቱ ድርጅት ከሞቃዲሾ ጎን እደሚቆምም አረጋግጠዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *