የባርሳ ደጋፊዎች የሜሲ ሶስት ጎሎች የክለቡ ታሪካዊ ምርጥ ጎል ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚ ናቸው ብለዋል
የካታላኑ ክለብ ባርሴሎና ደጋፊዎች የክለቡ የምንግዜም ምርጥ ጎሎችን ሲመረጡ የኮከባቸውን ሊዮኔል አንድሪያስ ሜሲ ሶስት ጎሎች፤ በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያው፣ ሁለተኛው እና ሶስተኛ ደረጃ እንሰጣቸዋለን ሲሉ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡
ቀዳሚ ደረጃን ያገኘችው ግብ፤ ባርሴሎና በ2006- 07 የስፔን ኮፓ ዴል ሬይ ከሄታፌ ጋር በተደረገው የግማሽ ፍፃሜ የባርሴሎና አጋማሽ ውስጥ ተነስቶ አራት ተከላካዮችን ገነዳድሶ፤ ከዚያም ግብ ጠባቂውን አልፎ ያስቆጠራት ግብ 45 በመቶ ድምፅ አግኝታለች፡፡
ይህቺ ጎል በ1986 አርጀንቲና ከ እንግሊዝ ጋር በነበራት ጨዋታ የሀገሩ ልጅ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ሶስቱ አናብስት መረብ ላይ ያሳረፋት ካርበን ኮፒ ነች፡፡
በ2014- 15 ኮፓ ዴል ሬይ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ከመረብ ያገናኛት ግብ በ28 በመቶ የደጋፊዎች ድምፅ ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ፤ በ2010- 11 የውድድር ዓመት ሳንቲያጎ ቤርናቤው ላይ በሪያል ማድሪድ መረብ የተቆጠረችው ግብ ደግሞ በ16 በመቶ የሶስተኛነት ደረጃን መያዝ ችላለች፡፡
ስፔናዊው ሰርጂ ሮቤርቶ ክለቡ ፓርክ ደፕሪንስ ላይ በፓሪስ ሴንት ዤርማ የደረሰበትን የ4 ለ 0 ሽንፈት ቀልብሶ ወደ ግማሽ ፍፃሜ በተሻገረበት የ2017ቱ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ባለቀ ሰዓት ያስቆጠራት ግብ አራተኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡
በድምፅ አሰጣጡ ከ160 ሀገራት የተወጣጡ 500 ሺ ደጋፊዎች በ63 ጎሎች ላይ ድምፅ ተሰጥቷል፡፡