የኦነግ ሰራዊት አባላትን ወደካምፕ ለማስገባት የቴክኒክ ኮሚቴው ወደተለያዩ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ ተገለጸ
የኦነግ ሰራዊት አባላትን ወደካምፕ ለማስገባት የቴክኒክ ኮሚቴው ወደተለያዩ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ ተገለጸ።
በኦነግና በመንግስት መካከል ለወረደው እርቀ ሰላም ማስፈጸሚያ የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ የሁለቱም ወገን ተወካዮች በተገኙበት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት የኦነግ ሰራዊት አባላትን ወደ ካምፕ ለማስገባት ወደ 12 ዞኖችና 22 የተመረጡ ወረዳዎች ስምሪት ይጀመራል።
ስምሪቱ ከረቡዕ የካቲት 6 ቀን ጀምሮ እንደካሄድ የተገለጸ ሲሆን ይህም ከየካቲተ 12 እስከ 14 ቀን ድረስ ሰራዊቱን አጠቃልሎ ካምፕ ለማስገባት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል ተብሏል።
የኦነግ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት ወደካምፕ እንዲገቡ ለማድረግ ድርጅታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ የተናገሩ ሲሆን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)ን ወክለው የተገኙት አቶ ሞገስ ኢደኤም በበኩላቸው የቴክኒክ ኮሚቴውና አባገዳዎቹ ዘላቂ እርቀ ሰላም ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
መንግስት ለኦሮሚያ ክልልም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲል ከኦነግ ባሻገር ካሉ ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ጋርም በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሞገስ፤ መላው ህዝብም የተጀመረው እርቀ ሰላም ከግብ ይደርስ ዘንድ በሙሉ ልቡ ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የአባ ገዳዎቹና ቴክኒክ ኮሚቴው ተወካይ አቶ ኃይሌ ገብሬ በበኩላቸው የአባገዳዎቹና የቴክኒከ ኮሚቴው ተልእኮ እንዲሳካ ሁለቱም ወገኖች ላሳዩት ተባባሪነትና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ።
በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሰራዊትን ወደ ካምፕ ከማስገባት ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች ተፈጥረው ከመቆየታቸው በተጨማሪ በተለይም በምእራብና ደቡብ ኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል።
የቴክኒክ ኮሚቴውም ይህንን ችግር ለመፍታት በኦነግ መሪዎች መካከል በተደረሰው የእርቅ ስምምነት ወቅት የኦነግን ሰራዊት ወደካምፕ እንዲያስገባ የተቋቋመ ነው።