የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ዕጣ ድልድል ይፋ ሁኗል
የ2018/19 ቶታል ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ፤ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዕጣ ድልድል በትናንትናው ዕለት በካፍ ፅ/ቤት መቀመጫ ካይሮ ይፋ ሁኗል፡፡
ለ23ኛ በሚካሄደው የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ሩብ ፍፃሜ ተፋላሚዎች ከየምድባቸው አንደኛ እና ሁለተኛ ሁነው ያለፉ ቡድኖች የሚሳተፉበት ሲሆን የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ፣ የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ፣ የቱኒዚያው ኤስፔራስ ዴ ቱኒስ፣ የጊኒው ሆሮያ፣ የዲ. ሪ ኮንጎው ቲፒ ማዜንቤ ፣ የአልጀሪያው ኮንስታንቲኖስ ፣ የግብፁ አል – አህሊ እና የታንዛኒያው ሲምባ ይካፈላሉ፡፡
በወጣው ዕጣ ሆሮያ ከ ዋይዳድ ካዛብላንካ፣ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከ አል- አህሊ፣ ኮንስታንቲን ከ ኤስፔራንስ እንዲሁም ሲምባ ከ ቲፒ ማዜምቤ ይጫወታሉ፡፡
በግማሽ ፍፃሜው የሆሮያ እና ዋይዳድ ካዛብላንካ አሸናፊ ከ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና አል- አህሊ አሸናፊ እንዲሁም የኮንስታንቲን እና ኤስፔራንስ ባለድል ከ ሲምባ እና ቲፒ ማዜምቤ አሸናፊ ጋር ይገናኛል፡፡
ለ16ኛ ጊዜ በሚካሄደው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ውድድር ደግሞ በሩብ ፍፃሜው የዛምቢያው ንካና ከ ቱኒዚያው ሰፋክሲያ፣ የቱኒዚያው ኢትዋል ዱ ሳሄል ከ ሱዳኑ አል- ሂላል፣ የሞሮኮው ሃሳኒያ አጋዲር ከ ግብፁ ዛማሊክ እንዲሁም የኬንያው ጎር ማሂያ ከ ሞሮኮው ቤርካኔ ጋር ይፋለማሉ፡፡
የንካና እና ሰፋክሲያ የበላይ ከኢትዋል ዱ ሳሄል እና አል- ሂላል አሸናፊ ጋር ፤ የሃሳኒያ አጋዲር እና የዛማሊክ የበላይ ከጎር ማሂያ እና ቤርካኔ አሸናፊ ጋር በግማሽ ፍፃሜው ተፋላሚ ይሆናሉ፡፡
የጥሎ ማለፉ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይከናወናሉ፡፡