ፖል ካጋሜ መከላከያችን ጠላትን ለማንበርከክ ዝግጁ ነው አሉ
ፖል ካጋሜ መከላከያችን ጠላትን ለማንበርከክ ዝግጁ ነው አሉ
አርትስ 03/04/11
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ የመከላከያ ጦራቸው የውጊያ ልምምድ በሚያደርግበት ማዕከል ተገኝተው ነው ይህን የተናገሩት፡፡
ካጋሜ ወታደሮቻቸውን በዚህ ልምምድ ያሳያችሁን ነገር ወታደራዊ ክህሎታችሁ ምን ያህል ከፍ ማለቱን ነው፤ የናንተ ጀግንነትና ቆራጥነት ለጠላቶቻችን እድል አይሰጣቸውም ብለዋቸዋል፡፡
ዛሬ ለልምምድ የምትተኩሷት አንዲት ጥይት ፣ ዋጋ እንዳላት ካሰባቸሁ ለጦር ሰራዊታችን የምናወጣው ሀብት ለትክክለኛ ዓላማ እንዲውል ታደርጉታላችሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በሀገራችን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን እንደ ጤናና ትምህርት የመሳሰሉ ዘርፎች እያሉ ለመከላከያ በርካታ ገንዘብ የምናወጣው የሉዓላዊነት ጉዳይ ስለሆነ ነው በማለትም አባላቱ ለቁጠባ ትኩረት እንዲሰጡ ካጋሜ አሳስበዋል፡፡
አሁን በዓለማችን ጀግንነትና ቆራጥነት ብቻቸውን በቂ አይደሉም፤ በእውቀትና በክህሎት የተካናችሁ መሆንም ያስፈልጋል ነው ያሏቸው ፡፡
ዘ ኒው ታይምስ እንደዘገበው ፕሬዝዳንቱ ለወታደሮቻቸው የሚከፍሏቸው ደሞዝ ሳይሆን የሀገራቸው ፍቅር ውጤታማ ስራ ለማከናወን እንዳስቻላቸው በአድናቆት ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ካጋሜ በመጨረሻም የሰራዊታችን ወቅታዊ አቋም በየትኛውም የጠላት ሀይል የማይደፈርና ሀገሩን በሚገባ የሚጠብቅ ስለመሆኑ አልጠራጠርም ብለዋል፡፡