የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ለአርትስ በላከዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዓለም ላይ የተከሰተውን የኮቪድ19 ወረርሽኝ ለመግታት የቻይና አፍሪካ ትብብር የማይተካ ሚና አለዉ ብለዋል የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ትናንት “ዓለም አቀፉ የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ኢኒሸቲቭ” የቪዲዮ ኮንፈረንስ በተካሄገበት ወቅት እንዳሉት ፤የዓለም ስጋት የሆነውን የኮቪድ19 ወረርሽኝ ለመግታት በቻይና እና አፍሪካ መካከል የሚደረገው ትብብር ከምንጊዜውም በላይ ወሳኝ ነዉ። ቻይና የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመግታት የተከተለችውን ስትራቴጂ እና የተገኘውን ውጤትም አድንቀዋል። ኢትዮጵያ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመግታት እያደረገች ባለው እንቅስቃሴ የቻይና መንግስት እና እንደ ጃክማ የመሳሰሉ የቻይና በለሃብቶች እያደረጉት ላለው ድጋፍ ያመሰገኑት አቶ ገዱ፥ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በኮንፈረንሱ ላይ የቻይና ስቴት ካውንስልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል። “የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ኢኒሸቲቭ” ዓለም አቀፍ ትብብርን በማሳደግ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመግታት የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በተመለከተ በስፋት መብራራቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት የላከልን መግለጫ ያመለክታል።